ዳንኤል 6:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዳርዮስ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ እንዲገዙ አንድ መቶ ሃያ መሳፍንትን መሾም ፈለገ፤

2. በእነዚህም ላይ ሦስት የበላይ አስተዳዳሪዎችን አደረገ፤ ከእነርሱም አንዱ ዳንኤል ነበረ። ንጉሡ ጒዳት እንዳይደርስበት፣ መሳፍንቱ ተጠሪነታቸው ለሦስቱ የበላይ አስተዳዳሪዎች እንዲሆን ተደረገ።

3. ከመሳፍንቱና ከበላይ አስተዳዳሪዎቹ ሁሉ ይልቅ ዳንኤል ልዩ የጥበብ መንፈስ የሞላበት ሆኖ በመገኘቱ፣ ንጉሡ በመላው ግዛቱ ላይ ሊሾመው አሰበ።

4. በዚህ ምክንያት የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ ዳንኤል በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ ሊከሱት ሰበብ ፈለጉ፤ ነገር ግን አላገኙበትም፤ ዳንኤል ታማኝ፣ ጠንቃቃና በሥራው እንከን የሌለበት ስለ ነበር፣ በእርሱ ላይ ስሕተት ሊያገኙ አልቻሉም።

5. እነዚህም ሰዎች፣ “ከአምላኩ ሕግ ጋር በተያያዘ ጒዳይ ካልሆነ በቀር፣ ይህን ሰው የምንከስበት ምንም ሰበብ አናገኝበትም” አሉ።

ዳንኤል 6