ዘፍጥረት 9:3-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ።

4. “ነገር ግን ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ።

5. ሰውን የገደለ ሁሉ ስለሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ፣ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ።

6. “የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ፣ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል፤በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) አምሳል፣እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን ሠርቶታልና።

7. እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ፤ ይንሠራፋ።”

8. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና አብረውት ያሉትን ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤

9. “እነሆ፤ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤

10. እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ከወፎች፣ ከቤት እንሰሳት፣ ከዱር እንስሳት፣ ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ።

ዘፍጥረት 9