ዘፍጥረት 29:23-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም አብሮአት ተኛ።

24. ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጡር እንድትሆን ሰጣት።

25. ሲነጋም እነሆ፤ ልያ ሆና ተገኘች፤ ስለዚህም ያዕቆብ ላባን፣ “ምነው፣ እንዲህ ጒድ ሠራኸኝ? ያገለገልኹህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው።

26. ላባም እንዲህ አለው፤ “በአገራችን ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤

27. ይህን የጫጒላ ሳምንት ፈጽምና፣ ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን።

28. ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋር ተሞሽሮ ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ፤ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት፤

29. ባላ የተባለች አገልጋዩንም ደንገጡር እንድትሆናት ለራሔል ሰጣት።

30. ያዕቆብ ከራሔልም ጋር ተኛ፤ ራሔልን ከልያ አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያም የተነሣ ሌላ ሰባት ዓመት ላባን አገለገለው።

31. እግዚአብሔር (ያህዌ) ልያ እንዳልተወደደች ባየ ጊዜ ማሕፀኗን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች።

32. ልያ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) መከራዬን ስለ ተመለከተልኝ፣ ከእንግዲህ ባሌ ይወደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል አለችው።

33. እንደ ገናም ፀንሳ ወለደች፤ እርሷም “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳልተወደድኩ ሰምቶ ይህን ልጅ በድጋሚ ሰጠኝ” አለች። ከዚያም የተነሣ ስምዖን ብላ ጠራችው።

ዘፍጥረት 29