9. ሙሴም ፈርዖንን፣ “በአባይ ወንዝ ካሉት በቀር ከአንተና ከቤቶችህ ጓጒንቸሮቹ እንዲወገዱ ለአንተ፣ ለሹማምቶችህና ለሕዝብህ የምንፀልይበትን ጊዜ እንድትወስን ለአንተ ትቸዋለሁ” አለው።
10. ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው። ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል።
11. ጓጒንቸሮቹም ከአንተና ከቤቶችህ፣ ከሹማምቶችህና ከሕዝብህ ተወግደው በዐባይ ወንዝ ብቻ ይወሰናሉ።”
12. ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ከተመለሱ በኋላ፣ በፈርዖን ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስላመጣቸው ጓጒንቸሮች ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ።
13. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጒንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየአጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ።
14. በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች።
15. ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።