24. የብር ወይም የናስ መባ ማቅረብ የቻሉ ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አድርገው አመጡ፤ የግራር ዕንጨት ያለው ሁሉ አስፈላጊ በሆነው ሥራ እንዲውል አመጣው።
25. ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ፤ የፈተሉትንም ሰማያዊ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን በፍታ አመጡ።
26. ፈቃደኛ የነበሩና ጥበቡ ያላቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ጠጒር ፈተሉ።
27. መሪዎቹም ኤፉድና በደረት ኪሱ ላይ እንዲሆን የከበሩ ድንጋዮችንና ሌሎች ዕንቍዎች አመጡ።
28. እንዲሁም ለመብራቱ፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ ሽታ ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞችንና የወይራ ዘይትን አመጡ።
29. ፈቃደኛ የሆኑ እስራኤላውያን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ በኩል እንዲያከናውኑት ላዘዛቸው ሥራ ሁሉ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አመጡ።
30. ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን አላቸው፤ “እነሆ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር ልጅ፣ የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጦአል።
31. በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማናቸውም ዐይነት ሙያ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መንፈስ ሞልቶበታል፤
32. ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በናስ የጥበብ ሥራ እንዲሠራ ነው፤
33. ድንጋዮችን እንዲጠርብና እንዲያወጣ፣ የዕንጨት ሥራ እንዲሠራና ማንኛውንም ዐይነት የጥበብ ሙያ እንዲያከናውን ነው።
34. እንዲሁም ለእርሱና ከዳን ነገድ ለሆነው ለአሂሳሚክ ልጅ ለኤልያብ፣ ለሁለቱም ሌሎችን የማስተማር ችሎታ ሰጣቸው።