ዘፀአት 23:21-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ አድምጠው፤ አታምፅበት። ስሜ በርሱ ላይ ነውና ዐመፅህን ይቅር አይልም።

22. የሚናገረውን በጥንቃቄ ብታደምጥና ያልኩህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህን እቃወማለሁ።

23. መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ አንተንም ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ያስገባሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ።

24. ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፤ ወይም አታምልካቸው፤ ወይም ልምዳቸውን አትከተል፤ እነርሱን ማፈራረስ አለብህ፤ የአምልኮ ድንጋዮቻቸውንም ሰባብር።

25. አምላክህን እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ።

26. በምድርህም የሚያስወርዳት ወይም መካን ሴት አትኖርም፤ ረጅም ዕድሜም እሰጥሃለሁ።

27. “በሚያጋጥሙህ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፤ ግራም አጋባቸዋለሁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ።

28. ኤዊያውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን ከመንገድህ ለማስወጣት ተርብን በፊትህ እሰዳለሁ።

ዘፀአት 23