14. “አንድ ሰው ከጎረቤቱ እንስሳ ተውሶ ሳለ ባለቤቱ በሌለበት ቢጎዳ ወይም ቢሞት ካሣ መክፈል አለበት።
15. ባለቤቱ ከእንስሳው ጋር ከሆነ ግን፣ ተበዳሪው መክፈል የለበትም፤ እንስሳው ከተከራየም ለኪራይ የተከፈለው ገንዘብ ኪሳራውን ይሸፍናል።
16. “አንድ ሰው ያልታጨችን ልጃገረድ አታልሎ ክብረ ንጽሕናዋን ቢያጎድል፣ የማጫዋን ዋጋ ከፍሎ ሚስት ያድርጋት።
17. እርሷን ለእርሱ የልጅቷ አባት በሚስትነት ለመስጠት ከቶ የማይፈቅድ ቢሆን፣ ለድንግሎች መከፈል የሚገባውን ማጫ አሁንም ቢሆን መክፈል ይገባዋል።
18. “መተተኛ ሴት በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድ።
19. “ከእንስሳ ጋር ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽም ሰው ይገደል።
20. “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በቀር ለሌላ አማልክት የሚሠዋ ይጥፋ።
21. መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብፅ መጻተኛ ነበራችሁና።
22. “ባል በሞተባት ወይም አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ።
23. ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ።
24. ቍጣዬ ይነሣል፤ በሰይፍም እገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ መበለቶች፣ ልጆቻችሁም አባት የለሽ ይሆናሉ።
25. “ከሕዝቤ መካከል ችግረኛ ለሆነው ለአንዱ ገንዘብ ብታበድሩ፣ እንደ አራጣ አበዳሪ አትሁኑ፤ ወለድ አትጠይቁት።
26. የጎረቤትህን ልብስ መያዣ አድርገህ ብትይዝ ሲመሽ መልስለት፤
27. ምክንያቱም ለሰውነቱ መሸፈኛ ያለው ልብስ ያ ብቻ ነው፤ ሌላ ምን ለብሶ ይተኛል? ወደ እኔ ሲጮህ እኔ እሰማለሁ፤ እኔ ርኅሩኅ ነኝና።
28. “በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ላይ የስድብ ቃል አታሰማ፤ ወይም የሕዝብህን መሪ አትርገም።