7. ስለዚህ ሙሴ አማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ዝቅ ብሎ እጅ በመንሣትም ሳመው፤ ከዚያም ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ ድንኳኑ ገቡ።
8. ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእስራኤል ሲል በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በመንገድም ላይ ስላጋጠማቸው መከራ ሁሉና እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዴት እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው።
9. ዮቶርም እግዚአብሔር (ያህዌ) እነርሱን ከግብፃውያን እጅ በመታደግ ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ሁሉ በመስማቱ ተደሰተ።
10. እንዲህም አለ፤ “ከግብፃውያን እጅና ከፈርዖን ለታደጋችሁ፣ ከግብፃውያን እጅ ሕዝቡን ለታደገ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ምስጋና ይሁን”።
11. “እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጎአልና።”