ዘፀአት 16:16-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጐሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዞአል።

17. እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ።

18. የሰበሰቡትን በጐሞር በሰፈሩ ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም ጥቂት የሰበሰበውም አልጐደለበትም እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ።

19. ሙሴም፣ “ማንም ከዚህ ለነገ ምንም ማስተረፍ የለበትም” አላቸው።

20. ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግሥቱም ጠዋት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው።

21. በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ።

ዘፀአት 16