ዘፀአት 10:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ።

5. አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል።

6. የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብፃውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ።

7. የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብፅ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን? አሉት።

8. ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ።

9. ሙሴም፣ “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ልናከብር ስለ ሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ።

10. ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋር እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር ይሁን ነገር ግን ተንኰል አስባችኋል።

11. አይሆንም ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱና እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ።

12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብፅ አገር ላይ ዘርጋ” አለው።

13. ስለዚህ ሙሴ በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) በዚያን ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግሥቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ።

14. እነርሱም ግብፅን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም።

ዘፀአት 10