ዘፀአት 10:15-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ፣ ጠርገው በሉ። በግብፅ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር።

16. ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ያህዌ) በእናንተም ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤

17. እንግዲህ አሁን አንድ ጊዜ ደግሞ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝና ይህንን ቀሣፊ መዓት እንዲያስወግድልኝ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለምኑልኝ።”

18. ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ።

19. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነፋሱን ወደ ብርቱ የምዕራብ ነፋስ ለወጠው ያም ነፋስ አንበጣዎቹን እየነዳ ወደ ቀይ ባሕር ከተታቸው፤ በግብፅ ምድር በየትኛውም ቦታ አንድም አንበጣ አልቀረም።

20. እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን እንዲሄዱ አልፈቀደም።

21. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በግብፅ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው።

22. ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው ግብፅ ላይ ለሦስት ቀናት ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሆነ።

23. በነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ አንዱ ሌላውን ማየት ወይም ከነበረበት ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበር።

24. ከዚያም ፈርዖን ሙሴን አስጠርቶ፣ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ሳይቀሩ አብረዋችሁ ይሂዱ፤ በጎቻችሁ፣ ፍየሎቻችሁና የጋማ ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቅሩ” አለው።

ዘፀአት 10