4. ከዚያ በኋላ የፈታት የመጀመሪያ ባሏ፣ የረከሰች በመሆኗ እንደ ገና መልሶ ሊያገባት አይችልም፤ ይህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አስጸያፊ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ኀጢአት አታምጣ።
5. አዲስ ሚስት በቅርብ ጊዜ ያገባ ሰው፣ ለጦርነት አይሂድ፤ ወይም ሌላ ሥራ እንዲሠራ አይገደድ። ለአንድ ዓመት ነጻ ሆኖ እቤቱ ይቈይ፤ ያገባትን ሚስቱን ደስ ያሰኛት።
6. ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም እንኳ ቢሆን፣ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ፤ የሰውን ነፍስ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆናልና።
7. አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፣ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።
8. የለምጽ ደዌን በተመለከተ ሌዋውያን ካህናት የሚሰጡህን መመሪያ በትክክል ለመፈጸም ጥንቃቄ አድርግ። እኔ ለእነርሱ የሰጠሁትን ትእዛዝ በጥንቃቄ ተከተል።
9. ከግብፅ ከወጣችሁ በኋላ በመንገድ ላይ ሳላችሁ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በማርያም ላይ ያደረገባትን አስታውሱ።