3. እነዚህም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ግንባር ፈጥረው በመምጣት፣ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም? የማኅበረ ሰቡ አባላት ሁሉ እያንዳንዳቸው የተቀደሱ ናቸው፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከእነርሱ ጋር ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ማኅበር ላይ የምትታበዩት ለምንድ ነው?” አሉአቸው።
4. ሙሴም ይህን ሲሰማ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤
5. ቆሬንና ተከታዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእርሱ የሆነውና የተቀደሰው ማን መሆኑን እግዚአብሔር (ያህዌ) ነገ ጠዋት ይለያል፤ ወደ ራሱም ያመጣዋል፤ የሚመርጠውን ሰው ወደ ራሱ እንዲቀርብ ያደርገዋል።
6. ቆሬ፣ አንተና ተከታዮችህ ሁሉ እንዲህ አድርጉ፤ ጥናዎችን ውሰዱ፤
7. በማግስቱም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እሳትና ዕጣን ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚመርጠውም ያ ሰው ቅዱስ ይሆናል፤ እናንት የሌዊ ልጆች፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ናችሁ።”