47. “ከበግ ጠጒር ወይም ከበፍታ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት ልብስ በተላላፊ በሽታ ቢበከል፣
48. በሸማኔ ዕቃ ወይም በእጅ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት የበግ ጠጒር ወይም የበፍታ ልብስ፣ ወይም ማንኛውም ቈዳ ወይም ከቈዳ የተሠራ ነገር ቢሆን፣
49. በልብስ ወይም በዐጐዛ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራ ወይም በእጅ በተጠለፈ ወይም ከቈዳ በተሠራ ዕቃ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ መሳይ ደዌ ቢከሠት፣ እየሰፋ የሚሄድ ተላላፊ በሽታ ስለ ሆነ ካህኑ ይየው።
50. ካህኑ ደዌውን ይመርምር፤ በደዌ የተበከለውንም ዕቃ ሰባት ቀን ያግልል።
51. በሰባተኛውም ቀን ይመርምረው፤ ደዌው በልብሱ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ወይም ለማናቸውም አገልግሎት በሚውል ዐጐዛ ላይ ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ ክፉ ደዌ ነው፤ ዕቃውም ርኩስ ነው።
52. ልብሱን ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራውን ወይም በእጅ የተጠለፈውን የበግ ጠጒር ወይም በፍታ ወይም ደዌው ያለበትን ማንኛውንም ከቈዳ የተሠራ ዕቃ ያቃጥል፤ ደዌው ክፉ ነውና፤ ዕቃው ይቃጠል።