ዘሌዋውያን 11:10-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ነገር ግን በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ከሚኖሩት ፍጡሮች ሁሉ፣ ከሚንፏ ቀቁት ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ሕይወት ካላቸው ሌሎች ፍጡሮች መካከል ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ፤

11. በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ስለሆኑ ሥጋቸውን አትብሉ፤ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ፤

12. ክንፍና ቅርፊት የሌለው ማንኛውም በውሃ ውስጥ የሚኖር ፍጡር በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ይሁን።

13. “ ‘ከአዕዋፍ ወገን እነዚህን ትጸየፋላችሁ፤ ጸያፍ ስለ ሆኑም አትብሏቸው፦ ንስር፣ ጥንብ አንሣ፣ ግልገል አንሣ፣

14. ጭላት፣ ማንኛውም ዐይነት ጭልፊት፣

15. ማንኛውም ዐይነት ቊራ፣

16. ሰጐን፣ ጠላቋ፣ ዝይ፣ ማንኛውም ዐይነት በቋል፣

17. ጒጒት፣ ርኩም፣ ጋጋኖ፣

18. የውሃ ዶሮ፣ ይብራ፣ ስደተኛ አሞራ፣

19. ሽመላ፣ ማንኛውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጅንጁላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ።

20. “ ‘ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ።

21. ነገር ግን ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር ከሚንቀሳቀሱ ነፍሳት መካከል ከምድር በሚፈናጠሩበት እግራቸው አንጓ ያለባቸውን መብላት ትችላላችሁ።

22. ከእነዚህ ማንኛውንም ዐይነት አንበጣ፣ ፌንጣና ኵብኵባ መብላት ትችላላችሁ።

23. ነገር ግን ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ተጸየፏቸው።

24. “ ‘ከእነዚህ የተነሣ ትረክሳላችሁ፤ የእነዚህን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኵስ ይሆናል።

25. የእነዚህንም በድን የሚያነሣ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።

26. “ ‘ሰኰና ያለው፣ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። የእነዚህንም በድን የሚነካ ሰው ሁሉ ይረክሳል።

27. አራት እግር ካላቸው እንስሳት ሁሉ በመዳፋቸው የሚሄዱት በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ በድናቸውንም የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኵስ ይሆናል።

ዘሌዋውያን 11