1. የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናዎቻቸውን ወስደው ፍም አደረጉባቸው፤ ዕጣንም ጨመሩባቸው፤ እርሱ ያላዘዛቸውን፣ ያልተፈቀደውን እሳት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረቡ።
2. ከዚህም የተነሣ እሳት ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ሞቱ።
3. ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ)፦‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣እከበራለሁ’ ብሎ የተናገረው ይህን ነው።”አሮንም ዝም አለ።
4. ሙሴ የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ፣ “ወደዚህ ኑና ወንድሞቻችሁን አንሡ፤ ከመቅደሱም ደጃፍ አርቃችሁ፣ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዷቸው” አላቸው።
5. እነርሱም መጥተው ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ ሟቾቹ የክህነት ቀሚሳቸውን እንደ ለበሱ ተሸክመው ከሰፈር ወደ ውጭ አወጧቸው።