ኤርምያስ 49:2-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ስለዚህ በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ፣የጦርነት ውካታ ድምፅ፣የሚሰማበት ጊዜ ይመጣል፤”ይላል እግዚአብሔር፤“እርሷም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤በዙሪያዋ ያሉት መንደሮችም ይቃጠላሉ፤እስራኤልም ከአገሯ ያስወጧትን፣ከአገሯ ታስወጣለች፤”ይላል እግዚአብሔር፤

3. ሐሴቦን ሆይ፤ ጋይ ጠፍታለችና ዋይ በይ፤የራባት ሴቶች ልጆች ሆይ ጩኹ፤ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ፤ሚልኮም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋር፣ተማርኮ ይወሰዳልና፣በቅጥር ውስጥ ወዲያ ወዲህ ተሯሯጡ።

4. አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፣በሸለቆችሽ ለምን ትመኪያለሽ?ለምንስ በፍሬያማ ሸለቆሽ ትኵራሪያለሽ?በብልጽግናሽ ተማምነሽ፣‘ማን ሊነካኝ ይችላል?’ ትያለሽ።

5. በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ፣ሽብር አመጣብሻለሁ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤“እያንዳንዳችሁ ትሰደዳላችሁ፤በሽሽት ላይ ያሉትንም የሚሰበስብ አይገኝም።

6. “ከዚያ በኋላ ግን፣ የአሞናውያንን ምርኮ እመልሳለሁ፣”ይላል እግዚአብሔር።

7. ስለ ኤዶም፤የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ጥበብ ከቴማን ጠፍቶአልን?ምክር ከአስተዋዮች ርቆአልን?ጥበባቸውስ ተሟጧልን?

ኤርምያስ 49