1. ኢየሩሳሌም የተያዘችው እንዲህ ነበር፤ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አሰልፎ በመምጣት ኢየሩሳሌምን ከበባት።
2. በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ አንደኛው ዓመት በአራተኛው ወር፣ በወሩም በዘጠነኛው ቀን የከተማዪቱ ቅጥር ተሰበረ።
3. የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ፦ የሳምጋሩ ኤርጌል ሳራስር፣ ዋና አዛዡ ናቦሠርሰኪም፣ ከፍተኛው ሹም ኤርጌል ሳራሳር እንዲሁም ሌሎቹ የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ ገብተው በመካከለኛው በር ተቀመጡ።