9. ስለ ነቢያት፣ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል፤ዐጥንቶቼም ተብረክርከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ፣ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ፣የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው፣እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ።
10. ምድሪቱ በአመንዝሮች ተሞልታለች፤ከርግማን የተነሣ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤በምድረ በዳ ያሉት መሰማሪያዎች ደርቀዋል።ነቢያቱም ጠማማ መንገድ ተከትለዋል፤ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል።
11. “ነቢዩም፣ ካህኑም በጽድቅ መንገድ የማይሄዱ ናቸው፤በቤተ መቅደሴ እንኳ ሳይቀር ክፋታቸውን አይቻለሁ።”ይላል እግዚአብሔር።
12. “ስለዚህ መንገዳቸው ድጥ ይሆናል፤ወደ ጨለማ ይጣላሉ፤ተፍገምግመውም ይወድቃሉ፤በሚቀጡበትም ዓመት፣መዓት አመጣባቸዋለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።
13. “በሰማርያ ባሉ ነቢያት ላይ፣ደስ የማያሰኝ ነገር አይቻለሁ፤በበኣል ስም ትንቢት ተናገሩ፤ሕዝቤን እስራኤልን አሳቱ።
14. በኢየሩሳሌም ባሉ ነቢያትም ላይ፣የሚዘገንን ነገር አይቻለሁ፤ያመነዝራሉ፤ በመዋሸትም ይኖራሉ፤ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ፣የክፉዎችን እጅ ያበረታሉ፤በእኔ ዘንድ ሁሉም እንደ ሰዶም፣ነዋሪዎቿም እንደ ገሞራ ናቸው።”