5. የዚህችን ከተማ ሀብት ሁሉ፣ ጥሪቷን፣ የይሁዳን ነገሥታት ውድ ዕቃና ንብረት ሁሉ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ዘርፈው ወደ ባቢሎን ይዘውት ይሄዳሉ።
6. ጳስኮር ሆይ፤ አንተና በቤትህ የሚኖሩት ሁሉ ወደ ባቢሎን ትጋዛላችሁ። አንተና በሐሰት ትንቢት የተነበይህላቸው ባልንጆሮችህ በዚያ ትሞታላችሁ፤ በዚያም ትቀበራላችሁ።’ ”
7. እግዚአብሔር ሆይ፤ አታለልኸኝ፤ እኔም ተታለልሁ፤አንተ ከእኔ እጅግ በረታህ፤ አሸነፍህም፤ቀኑን ሙሉ ማላገጫ ሆንሁ፤ሁሉም ተዘባበቱብኝ።
8. በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤“ሁከትና ጥፋት!” ብዬ ዐውጃለሁ፤ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል፣ቀኑን ሙሉ ስድብና ነቀፋ አስከተለብኝ።
9. ነገር ግን፣ “ከእንግዲህ የእርሱን ስም አላነሣም፤በስሙም አልናገርም” ብል፣ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤ዐፍኜ መያዝ አቃተኝ፤ጨርሶ መቋቋም አልቻልሁም።
10. “በየቦታው ሽብር አለ፤አውግዙት፤ እናውግዘው፤”ብለው ብዙ ሲያንሾካሽኩ ሰማሁ፤መውደቄን በመጠባበቅ፣ባልንጀሮቼ የነበሩ ሁሉ፣“ይታለል ይሆናል፣ከዚያም እናሸንፈዋለን፤እንበቀለዋለንም” ይላሉ።
11. ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ኀያል ተዋጊ ከእኔ ጋር ነው፤ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ እንጂ አያሸንፉም፤ክፉኛ ይዋረዳሉ እንጂ አይሳካላቸውም፤ውርደታቸውም ከቶ አይረሳም።
12. ጻድቁን የምትፈትን ልብንና አእምሮን የምትመረምር፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ጒዳዬን ለአንተ አሳልፌ ሰጥቻለሁናስትበቀላቸው ለማየት አብቃኝ።