1. ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤
2. “የዚህን ኪዳን ቃል ስማ፤ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሰዎች ንገራቸው፤
3. የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው፤ ‘ለዚህ ኪዳን ቃል የማይታዘዝ ሰው የተረገመ ይሁን፤
4. ይህም ትእዛዝ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር፣ ከብረት ማቅለጫው ምድጃ ባወጣኋቸው ጊዜ ድምፄን ቢሰሙ፣ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቁ፣ እነርሱ ሕዝቤ፣ እኔም አምላካቸው እንድሆን የሰጠኋቸው ቃል ነው፤