ኢያሱ 9:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዮርዳኖስ ምዕራብ ባለው በተራራማው አገር፣ በቈላማው ምድር እንዲሁም እስከ ሊባኖስ በሚደርሰው በመላው በታላቁ ባሕር ዳርቻ የነበሩት የኬጢያውያን፣ የአሞራውያን፣ የከነዓናውያን፣ የፌርዛውያን፣ የኤዊያውያን፣ የኢያቡሳውያን ነገሥታት ይህን በሰሙ ጊዜ፣

2. ኢያሱንና እስራኤልን ለመውጋት በአንድነት መጡ።

3. የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ላይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፣

4. ለማታለል ፈለጉ፤ ስለዚህም ያረጀ ስልቻና የተጣፈ አሮጌ የወይን ጠጅ አቊማዳ በአህያ የጫነጀ መልእክተኛ መስለው ሄዱ።

5. ሰዎቹም ያረጀና የተጠጋገነ ነጠላ ጫማ አድርገዋል፤ አሮጌ ልብስ ለብሰዋል፤ ለስንቅ የያዙት እንጀራም በሙሉ የደረቀና የሻገተ ነበር።

6. ከዚያም ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ኢያሱንና የእስራኤልን ሰዎች፣ “የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግቡ” አሏቸው።

7. የእስራኤልም ሰዎች ለኤዊያውያኑ፣ “እናንተ የምትኖሩት እዚሁ ቅርብ ቢሆንስ? ታዲያ ከእናንተ ጋር እንዴት ቃል ኪዳን እንገባለን?” አሏቸው።

ኢያሱ 9