1. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አወድሳለሁ፤አስቀድሞ የታሰበውን፣ድንቅ ነገር፣በፍጹም ታማኝነት አድርገሃልና።
2. ከተማዪቱን የድንጋይ ክምር አድርገሃታል፤የተመሸገችውንም ከተማ አፈራርሰሃታል፤የተመሸገችው የባዕድ ከተማ ከእንግዲህ አትኖርም፤ተመልሳም አትሠራም።
3. ስለዚህ ብርቱ ሕዝቦች ያከብሩሃል፤የጨካኝ አሕዛብ ከተሞችም ይፈሩሃል።
4. ለድኻ መጠጊያ፣በጭንቅ ጊዜ ለችግረኛ መጠለያ፣ከማዕበል መሸሸጊያ፣ከፀሓይ ትኵሳትም ጥላ ሆነሃል።የጨካኞች እስትንፋስ፣ከግድግዳ ጋር እንደሚላጋ ማዕበል ነውና፤