1. ከዚህም ነገር በኋላ ንጉሥ ጠረክሲስ የአጋጋዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከሌሎቹም መኳንንት ሁሉ ከፍተኛውን ሥልጣን በመስጠት አከበረው።
2. ንጉሡ ስለ እርሱ ይህ እንዲደረግለት አዞ ስለ ነበር፣ በንጉሡ በር ያሉት የመንግሥቱ ሹማምት ሁሉ ለሐማ ተንበርክከው እጅ በመንሣት አክብሮታቸውን ይገልጡለት ነበር። መርዶክዮስ ግን ወድቆ አልሰገደለትም፤ አክብሮትም አላሳየውም።
3. ታዲያ በንጉሡ በር ያሉት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን፣ “የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ?” ሲሉ ጠየቁት።
4. ይህንንም በየቀኑ ይነግሩት ነበር፤ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም። አይሁዳዊ መሆኑን ነግሮአቸው ስለ ነበር፣ የመርዶክዮስ ባሕርይ እስከ መቼ ሊቀጥል እንደሚችል ለማየት ሲሉ ይህንኑ ለሐማ ነገሩት።
5. ሐማም መርዶክዮስ ወድቆ እንዳልሰገደለትና እንዳላከበረው ሲያይ እጅግ ተቈጣ።
6. ይልቁንም መርዶክዮስ ከእነማን ወገን መሆኑን በተረዳ ጊዜ፣ መርዶክዮስን ብቻ መግደል እንደ ኢምንት ቈጠረው፤ ስለዚህ ሐማ በመላው የጠረክሲስ መንግሥት ውስጥ የሚገኙትንና የመርዶክዮስ ወገን የሆኑትን አይሁድ ሁሉ ለማጥፋት ዘዴ ፈለገ።