1. የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል፤በሃያኛው ዓመት ካሴሉ በተባለው ወር በሱሳ ግንብ ሳለሁ፣
2. ከወንድሞቼ አንዱ የሆነው አናኒ፣ ከሌሎች ጥቂት ሰዎች ጋር ከይሁዳ መጣ፤ እኔም ከምርኮ ስለተረፉት የአይሁድ ቅሬታዎችና ስለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኋቸው።
3. እነርሱም፣ “በሕይወት ተርፈው ከምርኮ ወደ አገራቸው የተመለሱት ሰዎች በታላቅ መከራና ውርደት ላይ ይገኛሉ፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈራርሶአል፤ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ።
4. ይህን ነገር በሰማሁ ጊዜ አያሌ ቀናት ዐዘንሁ፤ ጾምሁ፤ ጸለይሁም።