7. በቅጥር ውስጥ ዘጋብኝ፤ ስለዚህ ማምለጥ አልቻልሁም፤የእስር ሰንሰለቴንም አከበደብኝ።
8. ርዳታ ፈልጌ ብጣራና ብጮኽ እንኳ፣ጸሎቴን መስማት አልፈለገም።
9. መንገዴን በተጠረቡ ድንጋዮች ዘጋ፤ጐዳናዬንም አጣመመ።
10. አሸምቆ እንደ ተኛ ድብ፣እንደ አደባም አንበሳ፣
11. ከመንገድ ጐትቶ አስወጣኝ፤ ቈራረጠኝም፤ያለ ረዳትም ተወኝ።
12. ቀስቱን ገተረ፤ለፍላጻዎቹም ዒላማ አደረገኝ።
13. ፍላጻዎችን ከሰገባው አውጥቶ፣ልቤን ወጋው።
14. ለሕዝቤ ሁሉ ማላገጫ ሆንሁኝ፤ቀኑን ሙሉ በመሣለቅ ያዜሙብኛል።
15. መራራ ሥር አበላኝ፤ሐሞትም አጠገበኝ።
16. ጥርሴን በድንጋይ ሰበረ፤በትቢያ ውስጥ ረጋገጠኝ።
17. ነፍሴ ሰላምን አጣች፤ደስታ ምን እንደሆነ ረሳሁ።
18. ስለዚህ፣ “ክብሬ፣ ከእግዚአብሔርም ተስፋ ያደረግሁት ሁሉ ሄዶአል” አልሁ።
19. የጭንቀቴንና የመንከራተቴን፣ምሬትንና ሐሞትን አስባለሁ።
20. ዘወትር አስበዋለሁ፤ነፍሴም በውስጤ ተዋርዳለች።
21. ሆኖም ይህን አስባለሁእንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤
22. ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ርኅራኄው አያልቅምና።
23. ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ታማኝነትህም ብዙ ነው።
24. ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።
25. እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው።