1. “በሰርዴስ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ ሰባቱን የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱን ከዋክብት በእጁ የያዘው እንዲህ ይላል፤ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል።
2. ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም።
3. እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም።