44. አሳልፎ የሚሰጠውም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።
45. እንደ ደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው፤
46. ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት አሰሩትም።
47. በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ።
48. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቈመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን?
49. በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።”
50. በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተውት ሸሹ።
51. ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ያገለደመ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፣
52. ግልድሙን ጥሎ ዕራቍቱን ሸሸ።
53. ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሓፍት ሁሉ ተሰበሰቡ።
54. ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፣ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር።
55. የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም።
56. ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፣ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም።
57. አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤
58. “ይህ፣ ‘የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።”
59. ይህም ሆኖ፣ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም።
60. ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፣ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድን ነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው።
61. ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም።ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ የቡሩኩ ልጅ፣ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው።