1. ከዚያም እኔ እንዲህ አልሁ፤“እናንት የያዕቆብ መሪዎች፤እናንት የእስራኤል ቤት ገዦች ስሙ፤ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን?
2. መልካሙን ጠላችሁ፤ ክፉውንም ወደዳችሁ፤የሕዝቤን ቈዳ ገፈፋችሁ፤ሥጋቸውንም ከዐጥንቶቻቸው ለያችሁ፤
3. የሕዝቤን ሥጋ በላችሁ፤ቈዳቸውን ገፈፋችሁ፤ዐጥንቶቻቸውንም ሰባበራችሁ፤በመጥበሻ እንደሚጠበስ፣በድስት እንደሚቀቀል ሥጋ ቈራረጣችኋቸው።
4. እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፤እርሱ ግን አይመልስላቸውም፤ካደረጉት ክፋት የተነሣ፣በዚያ ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።