መዝሙር 125 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር የሚታመኑበትን ይጠብቃል

መዝሙረ መዓርግ

1. በእግዚአብሔር የሚታመኑ፣ሳትናወጥ ለዘላለም እንደምትኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው።

2. ተራሮች ኢየሩሳሌምን እንደ ከበቧት፣ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው።

3. ጻድቃን እጃቸውን፣ ለክፋት እንዳያነሡ፣የክፉዎች በትረ መንግሥት፣ለጻድቃን በተመደበች ምድር ላይ አያርፍም።

4. እግዚአብሔር ሆይ፤ መልካም ለሆኑ፣ልባቸውም ለቀና መልካም አድርግ።

5. ወደ ጠማማ መንገዳቸው የሚመለሱትን ግን፣ እግዚአብሔር ከክፉ አድራጊዎች ጋር ያስወግዳቸዋል።በእስራኤል ላይ ሰላም ይውረድ።