1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አዙር፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤
3. እንዲህም በል፤ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፤ ለገደላገደሎችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ የማምለኪያ ኰረብቶቻችሁን አጠፋለሁ።
4. መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሰባበራሉ፤ የታረዱ ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ።
5. የእስራኤላውያንን ሬሳ በጣዖቶቻችሁ ፊት አጋድማለሁ፤ ዐጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።
6. መሠዊያዎቻችሁ እንዲፈራርሱና እንዲወድሙ፣ ጣዖቶቻችሁ እንዲሰባበሩና እንዲደቁ፣ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁ እንዲንኰታኰቱ፣ የእጆቻችሁም ሥራ እንዲደመሰስ፣ የምትኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ ማምለኪያ ኰረብቶችም እንዳልነበሩ ይሆናሉ።