ሕዝቅኤል 37:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እንዲህም ይላሉ፤ ‘ዐጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋ የለንም፤ ተቈርጠናል።”

12. ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤ ከውስጣቸው አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ።

13. ከዚያም እናንተ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን ከፍቼ ሳወጣችሁ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

14. መንፈሴን በውስጣችሁ አስቀምጣለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤ በገዛ ምድራችሁ አስቀምጣችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ፣ እንዳደረግሁትም ታውቃላችሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።” ’

15. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

16. “የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ በትር ወስደህ፣ ‘የይሁዳና የተባባሪዎቹ የእስራኤላውያን’ ብለህ ጻፍበት። ከዚያም ሌላ በትር ወስደህ፣ ‘የኤፍሬም፣ የዮሴፍና የተባባሪዎቹ የእስራኤል ቤት ሁሉ’ ብለህ ጻፍበት።

17. እንደ አንድ በትር ይሆኑ ዘንድ በእጅህ ላይ አጋጥመህ ያዛቸው።

18. “የአገርህ ልጆች፣ ‘ይህስ ምን ማለትህ እንደሆነ አትነግረንምን?’ ብለው ሲጠይቁህ፣

19. እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትርና የተባባሪዎቹን የእስራኤላውያንን ነገድ በትር እወስዳለሁ፤ ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥሜ አንድ ወጥ በትር አደርጋቸዋለሁ፤ እነርሱም በእጄ አንድ በትር ይሆናሉ።’ ”

ሕዝቅኤል 37