6. ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በሌሎች ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ።
7. ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያህል ነበሩ።
8. ጳውሎስም ወደ ምኵራብ እየገባ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያሳመናቸው ሦስት ወር ሙሉ ምንም ሳይፈራ ፊት ለፊት ይናገር ነበር።
9. አንዳንዶቹ ግን ግትር በመሆን፣ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም፤ የጌታንም መንገድ በገሃድ ያጥላሉ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ትቶአቸው ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ የትምህርት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያነጋግራቸው ነበር።
10. ይህን ማድረጉንም ሁለት ዓመት ስለ ቀጠለ፣ በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ።
11. እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ታምራትን ያደርግ ነበር፤
12. መሐረብ ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታቸው ይለቃቸው ነበር፤ ርኵሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር።
13. እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዛችኋለሁ” እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኵሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤
14. የአይሁዳዊው የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር።
15. ርኩስ መንፈሱም፣ “ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተ ግን እነማን ናችሁ?” አላቸው።
16. ከዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቁታቸውን ሸሹ።
17. ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት፣ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ሁሉ ዘንድ በታወቀ ጊዜ፣ ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ።
18. ካመኑትም ሰዎች ብዙዎቹ እየቀረቡ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ ተናዘዙ፤
19. ሲጠነቁሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ አምሳ ሺህ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ።
20. በዚህ ሁኔታ የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ።
21. ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል ዐልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ ወስኖ፣ “እዚያ ከደረስሁ በኋላ ሮምን ደግሞ ማየት አለብኝ” አለ።
22. ከረዳቶቹም ሁለቱን፣ ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን፣ ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ ግን በእስያ አውራጃ ጥቂት ቀን ተቀመጠ።
23. በዚህ ጊዜ፣ ስለ ጌታ መንገድ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ።
24. ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች ከብር ቀጥቅጦ እየሠራ ለሠራተኞቹ የሚያስገኘው ገቢ ቀላል አልነበረም።
25. እርሱም እነዚህን ሠራተኞችና በተመሳሳይ ሙያ የሚተዳደሩትን ሌሎቹን ሰዎች በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ሆይ፤ ይህ ሥራ ጥሩ ገቢ እንደሚያስገኝልን ታውቃላችሁ።
26. ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የእስያ አውራጃ የሚገኘውን በርካታ ሕዝብ እያሳመነ እንዳሳታቸው ይኸው የምታዩትና የምትሰሙት ነገር ነው፤ በሰው እጅ የተሠሩ አማልክት በፍጹም አማልክት እንዳልሆኑ ይናገራልና።