26. እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ለማየት ይሆን? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ለማየት የወጣችሁት ከነቢይም የሚበልጠውን ነው።
27. እንዲህ ተብሎ የተጻፈለትም እርሱ ነው፤ “ ‘መንገድህን በፊትህ የሚያስተካክል፣ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ።’
28. እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።”
29. ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ይህን የሰሙ ሁሉ፣ የዮሐንስን ጥምቀት በመጠመቅ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር ሰጡት፤
30. ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎች ግን በዮሐንስ እጅ ባለ መጠመቃቸው፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዐላማ አቃለሉ።
31. ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን ልመስላቸው? ምንስ ይመስላሉ?
32. በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤ “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም።’
33. ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይ በላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤
34. የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፣ ‘በላተኛና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና “የኀጢአተኞች” ወዳጅ’ አላችሁት።
35. እንግዲህ የጥበብ ትክክለኛነት በልጆቿ ሁሉ ዘንድ ተረጋገጠ።”
36. ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ ምግብ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ጋበዘው፤ እርሱም ወደ ፈሪሳዊው ቤት ሄዶ በማእድ ተቀመጠ።
37. በዚያ ከተማ የምትኖር አንዲት ኀጢአተኛ ሴት፣ ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት በማእድ መቀመጡን በሰማች ጊዜ አንድ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ሽቶ ይዛ መጣች፤
38. ከበስተ ኋላው እግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች እግሩን በእንባዋ ታርስ፣ በራሷም ጠጒር ታብሰው ጀመር፤ እግሩንም እየሳመች ሽቱውን ቀባችው።
39. የጋበዘውም ፈሪሳዊ ይህን ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፣ የነካችው ሴት ማን እንደሆነች፣ ደግሞም ምን ዐይነት ሰው እንደሆነች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና” ብሎ በልቡ አሰበ።
40. ኢየሱስም፣ “ስምዖን ሆይ፤ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው።እርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ንገረኝ” አለው።
41. ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንደኛው አምስት መቶ ዲናር፣ ሁለተኛው ደግሞ አምሳ ዲናር ነበረበት።