2 ዜና መዋዕል 5:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠራው ሥራ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፣ ዕቃዎቹንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አኖራቸው።

2. ከዚያ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የየነገዱን መሪዎች ሁሉና የእስራኤላውያንን የቤተ ሰብ አለቆች በኢየሩሳሌም ሰበሰበ።

3. የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ የሰባተኛው ወር በዓል በሚከበርበት ጊዜ፣ በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ።

4. የእስራኤል ሽማግሌዎች በተሰበሰቡም ጊዜ ሌዋውያኑ ታቦቱን አነሡት፤

5. ታቦቱን፣ የመገናኛ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን የተቀደሱ ዕቃዎች ሁሉ ይዘው ወደ ላይ ወጡ፤ ሌዋውያን የሆኑ ካህናትም ተሸከሟቸው።

6. ንጉሥ ሰሎሞንና በአጠገቡ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ ስፍር ቊጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች በታቦቱ ፊት ሠዉ።

2 ዜና መዋዕል 5