2 ቆሮንቶስ 1:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. መከራ ብንቀበል ስለ እናንተ መጽናናትና መዳን ነው። ብንጽናናም እኛ የተቀበልነውን መከራ በመቀበል በትዕግሥት እንድትጸኑ ስለ እናንተ መጽናናት ነው።

7. ስለ እናንተ ያለን ተስፋ ጽኑ ነው፤ ምክንያቱም በመከራችን እንደ ተካፈላችሁ ሁሉ በመጽናናታችንም እንደምትካፈሉ እናውቃለን።

8. ወንድሞች ሆይ፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር።

9. በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው።

10. እርሱ እንዲህ ካለው የሞት አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ወደ ፊትም ደግሞ እንደሚያድነን ተስፋችንን በእርሱ ላይ ጥለናል።

11. እናንተም በጸሎታችሁ ደግፉን፤ በብዙዎች ጸሎት ስለ ተሰጠን ስጦታ ብዙ ሰዎች ስለ እኛ ምስጋና ያቀርባሉ።

12. እንግዲህ ትምክህታችን ይህ ነው፤ በዚህ ዓለም በተለይም ከእናንተ ጋር ባለን ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር በሆነ ቅድስናና ቅንነት እንደኖርን ኅሊናችን ይመሰክራል፤ ይህም በሰው ጥበብ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ነው።

13. ልታነቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን ነገር አንጽፍላችሁም፤ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ።

14. እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንደምንመካ አሁን የተረዳችሁን በከፊል ቢሆንም፣ በጌታ ኢየሱስ ቀን ሁሉን ትረዳላችሁ።

15. በዚህ ርግጠኛ ስለ ነበርሁ በዕጥፍ እንድትጠቀሙ፣ በመጀመሪያ ልጐበኛችሁ ዐቅጄ ነበር።

2 ቆሮንቶስ 1