9. በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤
10. የራሱ የሆነ መኖሪያ እንዲኖረውና ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይናወጥ፣ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጠዋለሁ፤ አጸናዋለሁም። ከዚህ በፊት እንደሆነውም ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቍነውም፤
11. ለሕዝቤ ለእስራኤልም መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ እንዳደረጉበት ሁሉ ከእንግዲህ አያደርጉበትም፤ እንዲሁም ከጠላቶችህ ሁሉ እጠብቅሃለሁ። “ ‘እግዚአብሔር ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤
12. ዕድሜህን ጨርሰህ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀ ላፋበት ጊዜ፣ በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።
13. ለስሜ ቤት የሚሠራ እርሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።
14. አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል። በደል ቢፈጽም ግን ሰዎች በሚቀጡበት በትር እቀጣዋለሁ፤ የሰው ልጆችም በዐለንጋ እንደሚገረፉ እገርፈዋለሁ።
15. ምሕረቴን ከአንተ በፊት ካስወገድሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ሁሉ ከእርሱ አላርቅም።
16. ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።’ ”
17. ናታንም የዚህን የጠቅላላውን ራእይ ቃል በሙሉ፣ ለዳዊት ነገረው።
18. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤“ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ ኧረ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው?
19. ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ አንተ ግን ስለ ወደፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ፤ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው?
20. “ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህና!
21. ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ባሪያህም እንዲያውቀው ገልጸህለታል።