7. አሁን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ምንጊዜም ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ፣ መንግሥቱን ለዘላለም አጸናታለሁ’።
8. “እንግዲህ አሁንም ይህቺን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት አድርጋችሁ እንድታወርሱአቸው፣ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ እንድታከብሩ በእስራኤል ሁሉ ፊት፣ በእግዚአብሔር ጉባኤና እግዚአብሔርም እየሰማ አዛችኋለሁ።
9. “አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውከው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል።
10. ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ እግዚአብሔር የመረጠህ መሆኑን አሁንም ዐስብ፤ በርትተህም ሥራ።
11. ከዚያም ዳዊት የቤተ መቅደሱን መመላለሻ፣ የሕንጻውን፣ የዕቃ ቤቶቹን፣ የፎቁንና የውስጥ ክፍሎቹን እንዲሁም የማስተስረያውን ቦታ ንድፍ ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው።
12. ደግሞም መንፈስ ቅዱስ በልቡ ያሳደረውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አደባባይ፣ በዙሪያው ያሉትን ክፍሎች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ ቤቶችና የንዋየ ቅድሳቱን ግምጃ ቤቶች ንድፍ ሁሉ ሰጠው፤