1. ዳዊት ከቂስ ልጅ ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በጺቅላግ ሳለ ወደ እርሱ የመጡት ሰዎች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም በጦርነቱ ላይ ከረዱት ተዋጊዎች መካከል ነበሩ።
2. ሰዎቹ ቀስተኞች ሲሆኑ፣ በቀኝም ሆነ በግራ እጃቸው ፍላጻ መወርወርና ድንጋይ መወንጨፍ የሚችሉ ነበሩ፤ እነርሱም ከብንያም ነገድ የሆነው የሳኦል ሥጋ ዘመዶች ነበሩ፤
3. አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፤ ከእርሱም በኋላ ኢዮአስ ነበረ፤ ሁለቱም የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች ነበሩ፤ የዓዝሞት ልጆች ይዝኤልና ፋሌጥ፤ በራኪያ፣ ዓናቶታዊው ኢዩ፤
4. ገባዖናዊው ሰማያስ ከሠላሳዎቹ መካከል ኀያልና የሠላሳዎቹም መሪ ነበረ፤ ኤርምያስ፣ የሕዚኤል፣ ዮሐናን፣ ገድሮታዊው ዮዛባት፣