27. እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ዐሥር ባለ መንኰራኵር የዕቃ ማስቀመጫዎች ከመዳብ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ርዝመት አራት ክንድ፣ ወርድ አራት ክንድ፣ ቁመትም ሦስት ክንድ ነበር።
28. የዕቃ ማስቀመጫዎቹ የተሠሩት እንደዚህ ነው፤ እነዚህም ቀጥ ብለው ከቆሙ ደጋፊዎች ጋር የተያያዙ ባለ አራት ማእዘን ጠፍጣፋ ናሶች ነበሯቸው።
29. ዳርና ዳር ባሉት ድጋፎች መካከል በሚገኙት ጠፍጣፋ ናሶች ላይ የአንበሶችን፣ የኮርማዎችንና የኪሩቤልን ምስል አደረገ፤ በድጋፎቹም ላይ እንደዚሁ አደረገ። ከአንበሶቹና ከኮርማዎቹ በላይና በታች በኩል ደግሞ የአበባ ጒንጒን የሚመስሉ ተቀጥቅጠው የተሠሩ ቅርጾች ነበሩ።
30. እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት የናስ መንኰራኵርና መንኰራኵሮቹ የሚሽከረከሩባቸው የናስ ወስከምቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው በአራቱም ማእዘን ገጽ ላይ የአበባ ጒንጒን ቀልጦ የተሠራባቸው የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበረው።
31. በዕቃ ማስቀመጫወቹም ውስጥ ጥልቀቱ አንድ ክንድ የሆነ ባለ ክብ ክፍተት ነበር፤ ይህም ክፍተት ድቡልቡል ሆኖ ከታች ከመቆሚያው በኩል ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ወርድ ሲኖረው፣ በክፍተቱም ዙሪያ ቅርጾች ነበሩ፤ ክፈፎቹ ግን ባለ አራት ማእዘን እንጂ ክብ አልነበሩም።