1. ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ሲል ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ፤
2. “ከትቢያ አንሥቼ፣ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ ሕዝቤ እስራኤል ኀጢአት እንዲሠራ፣ በኀጢአቱም ለቊጣ እንዲያነሣሣኝ አሳሳትኸው።
3. ስለዚህ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርገዋለሁ።
4. በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞቱትን የባኦስን ወገኖች ሁሉ ውሾች ይበሏቸዋል፤ በገጠር የሚሞቱትንም ሁሉ የሰማይ አሞሮች ይቀራመቷቸዋል።”
5. በባኦስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ ሌላው ያደረገው ሥራው በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
6. ባኦስ፣ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቴርሳም ተቀበረ። ልጁም ኤላ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።