1 ቆሮንቶስ 7:14-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፤ ያላመነችም ሚስት በሚያምን ባሏ ተቀድሳለች፤ አለዚያማ ልጆቻችሁ ርኩሳን በሆኑ ነበር፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው።

15. ነገር ግን የማያምነው ወገን መለየት ከፈለገ ይለይ፤ አንድ ወንድም ወይም እኅት በዚህ ሁኔታ የታሰሩ አይደሉም፤ እግዚአብሔር የጠራን በሰላም እንድንኖር ነው።

16. አንቺ ሴት፤ ባልሽን ታድኚው እንደሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ሰው፤ ሚስትህን ታድናት እንደሆነ ምን ታውቃለህ?

17. ብቻ እያንዳንዱ ሰው ጌታ እንደ ወሰነለት፣ እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው በዚያው ይመላለስ። በአብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ የምንደነግገው ይህንኑ ነው።

18. አንድ ሰው ተገርዞ ሳለ ቢጠራ፣ እንዳልተገረዘ ሰው አይሁን፤ ሳይገረዝም ተጠርቶ ከሆነ አይገረዝ።

19. መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸሙ ነው።

20. እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ጸንቶ ይኑር።

21. በተጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርህን? በዚህ አትጨነቅ፤ ነጻነትህን ማግኘት ከቻልህ ግን ነጻነትህን ተቀበል።

22. ምክንያቱም ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ፣ የጌታ ነጻ ሰው ነው፤ እንዲሁም ሲጠራ ነጻ የነበረ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው።

23. በዋጋ ተገዝታችኋል፤ ስለዚህ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ።

24. ወንድሞች ሆይ፤ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋር ጸንቶ ይኑር።

25. ስለ ደናግል፣ ከጌታ የተቀበልሁት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ምሕረት የተነሣ እንደ ታማኝ ሰው፣ ምክሬን እሰጣለሁ።

26. አሁን ካለው ችግር የተነሣ ባላችሁበት ሁኔታ ብትኖሩ መልካም ይመስለኛል።

27. አግብተህ ከሆነ መፋታትን አትሻ፤ ካላገባህም ሚስት ለማግባት አትፈልግ።

28. ብታገባ ግን ኀጢአት አልሠራህም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኀጢአት አላደረገችም። ነገር ግን የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፤ እኔም ይህ እንዳይደርስባችሁ እወዳለሁ።

29. ወንድሞች ሆይ፤ ሐሳቤ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ ዐጭር ነው፤ ከእንግዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ሆነው ይኑሩ።

30. የሚያለቅሱ እንደማያለቅሱ፣ ደስተኞች ደስ እንደማይላቸው ይሁኑ፤ ዕቃ የሚገዙም የገዙት ነገር የእነርሱ እንዳልሆነ ይቍጠሩ፤

31. በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደ ማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም መልክ ዐላፊ ነውና።

32. እኔስ ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን ደስ ለማሰኘት ስለ ጌታ ነገር ያስባል፤

33. ያገባ ሰው ግን ሚስቱን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ያስባል፤

1 ቆሮንቶስ 7