1 ሳሙኤል 31:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወጉ፤ እስራኤላውያን ከፊታቸው ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተወግተው ወደቁ።

2. ፍልስጥኤማውያን ሳኦልንና ልጆቹን አጥብቀው ተከታተሉ፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፣ አሚናዳብንና ሜልኪሳን ገደሉ።

3. ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም ደርሰው እጅግ አቈሰሉት።

4. ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች መጥተው እንዳይወጉኝ፣ እንዳያዋርዱኝ፣ አንተው ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው።ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፣ እምቢ አለው። ስለዚህ ሳኦል የራሱን ሰይፍ ወስዶ በላዩ ላይ ወደቀበት።

5. ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ባየ ጊዜ፣ እርሱም እንደዚሁ በሰይፉ ላይ ወድቆ አብሮት ሞተ።

6. ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ፣ አብረውት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ጋሻ ጃግሬው የሞቱት በዚያኑ ቀን ነበር።

7. በሸለቆው ማዶና ከዮርዳኖስ ባሻገር ያሉ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰራዊት መሸሹን፣ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።

1 ሳሙኤል 31